ጋዜጠኛው በድጋሚ መታፈኑ!

 ethiopian human right commussion
02 July 2022

by Dawit Atreso

ከቀናት በፊት ሲቪል በለበሱ ሰዎች ከቤቱ የተወሰደው ጋዜጠኛ ያየሰው ሽመልስ እስካሁን ያለበትን ማወቅ እንዳልቻሉ ቤተሰቦቹ ገለፁ። ቤተሰቦቹ ዛሬ በላኩልን መልዕክት ሰኔ 21 ቀን 2014 ዓ/ም 7 ሲቪል የለበሱ ሰዎች ከቤቱ ከወሰዱት በኃላ እስካሁን ድረስ ያለበትን ለማወቅ እንዳልቻሉ አስረድተዋል። " ፌዴራል ፖሊስ እና አዲስ አበባ ፖሊስ ብንፈልገውም ልናገኘው አልቻልም ፤ ለኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ብናመለክትም ከፌዴራል ፖሊስ እና አዲስ አበባ ፖሊስ ውጭ እንደሆኑ ነው የነገረን " ሲል አሳውቆናል ሲሉ ገልፀዋል። ቤተሰቦች በያየሰው ሽመልስ ቦታ አለመታወቅ ከፍተኛ ጭንቀት ላይ መሆናቸውን ገልፀው የወሰዳቸው አካል ያለበትን ብቻ እንዲያሳውቃቸው ተማፅነዋል።

ጋዜጠኛ ያየሰው ከጥቂት ቀናት በፊት ነበር በ10 ሺ ብር ዋስ ፍርድ ቤት ከእስር እንዲለቀቅ ወስኖለት የተለቀቀው። ከዚህ በኃላ ነው በድጋሚ የተያዘው። በተመሳሳይ ጋዜጠኛ ያየሰው ሽመልስ በተወሰደ ከአንድ ቀን በኃላ ጋዜጠኛ አበበ ባዩ ምሽት 4:30 ሲቪል በለበሱ ሰዎች የተወሰደ ሲሆን ቤተሰቦቹ እሱንም እካሁን ማግኘት እንዳልቻሉ አመልክተዋል። ፌዴራል ፖሊስ እና አ/አ ፖሊስ መጠየቃቸውን ነገር ግን እንዳላገኙት ፤ ያለበትን ለማወቅም ለኢሰመኮ ቢያመለክቱም ያለበትን ለማግኘት እንዳልተቻለ ገልፀዋል። የአበበ ባዩ ቤተሰቦችም ጭንቀት ላይ መሆናቸውን ገልፀው የወሰዳቸው አካል ያለበትን ቦታ እንዲያሳውቃቸው ተማፅነዋል። ጋዜጠኛ አበበ ባዩ ከጥቂት ወራት በፊት ለእስር ተዳርጎ መፈታቱ የሚታወስ ነው።